አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለተጸነሰባት ለዚያች ሰዐት ለዚያች ቀን ምስጋና ይገባታል።
ኢዮብ መከራ በገጠመው ጊዜ የተወለደበትን ቀን ረገመ፤ “ያ የተወለድሁበት ቀን ይጥፋ፥ ያም ወንድ ልጅ ተጸነሰ የተባለበት ሌሊት። ያ ቀን ጨለማ ይሁን እግዚአብሔር ከላይ አይመልከተው፤ ብርሃንም አይብራበት” ኢዮ. 3፥3 አለ።
እኛ ደግሞ ደስታችን ለጀመረባት ለዚህች ቀን ምስጋና እናቀርብላታለን።
ድንግል በድንግልና ሳለች ለፀነሰችበት ለዚህ ቀን አንክሮ ይገባል። ይህች ቀን ከዕለታት ተለይታ እስከ ዘለዓለም የከበረች ትሁን። በመጀመሪያም ዓለም የተፈጠረባት ቀን ነበረች። ዛሬ ደግሞ አዲሱ ዓለም በክርስቶስ ኢየሱስ ዳግመኛ ተፈጠረ።
አምላክ ሰው ለሆነባት ለዚህች ቀን ምን ዐይነት ምሳሌ ልናመጣላት እንችላለን?
ፀሐይ ጨረቃ በተፈጠሩበት በዕለተ ረቡዕ እንመስላት? ወይስ አዳም በተፈጠረባት በዕለተ ዐርብ?
ከፍ ብለን ሰማይ ዝቅ ብለን ምድር በተፈጠሩባት በዕለተ እሑድ ወይስ ተራሮችና ኮረብቶች በአበባ ባጌጡባት በዕለተ ሰሉስ? በየትኛዋ ቀን ልንመስላት እንችላለን? እነዚህ ሁሉ ምሳሌዎቿ ሊሆኑ የማይገባት ታላቅ ቀን ናት።
አምላክ ሰው ሲሆን ሰውም አምላክ ሆኗልና ይህች ቀን በሰው ልጆች ታሪክ ውስጥ ታላቅ ቀን ናት። ቀድሞ ከተፈጠርንባት ቀን ይልቅ የከበረች ናት።
በቀደመው ተፈጥሯችን መንበር ኪሩባዊትን የሚያወርስ ተፈጥሮ አልነበረንምና።
ኪሩቤል የሚሸከሙት ዙፋን በምድራዊት ሴት በማርያም ማኅጸን ለተዘረጋባት ለዚህች ቀን ክብር ይገባታል፤ ሰማይን ወደ ምድር ያወረደች ምድርን ወደ ሰማይ ያሳረገች እንደምን ያለች መደነቅ የሞላባት ቀን ናት? ያዕቆብ መላእክት ሲወጡና ሲወርዱ ካየባት ቀን ይልቅ ትበልጣለች፤ ያችኛዋ በሕልም እንጂ በእውነት መላእክት ሲወጡና ሲወርዱ የታዩባትን መሰላል ለያእቆብ ማስያዝ ስላልቻለች ነው።
የዛሬዋ ቀን ግን መሰላሏ በመካከላችን ተተክላ መላእክት ሲወጡባትና ሲወርዱባት ተመለከትናት።
ዛሬ የያዕቆብን መሰላል በመካከላችን አገኘናት፤ ከዕንቅልፋችን ሳይሆን ከኃጢአት ነቅተን መላእክት ለምስጋና ሲወጡባትና ሲወርዱባት ተመለከትናት።
የመላእክትን መውጣትና መውረድ ሊቃውንቱ ሲተረጉሙት ወደ ላይ መውጣታቸው ሰው አምላክ ሆነ፤ ወደታች መውረዳቸው አምላክ ሰው ሆነ ሲሉ ነው ብለው ተርጉመውታል። ንባቡን ሳይሆን ትርጓሜውን በመጽሐፍ ሳይሆን በተግባር እነሆ እየተመለከትነው ነው።
ነቢዩ ዳንኤል የሰው እጅ ሳይነካው ከረጅም ተራራ ተፈንቅሎ ሲወርድ ያየውን ድንጋይ ዛሬ በዐይናችን አየነው። ረጅሟ ተራራ እመቤታችን ናት፤ የሰው እጅ ያልነካው ድንጋይ ያለ ዘርዐ ብእሲ ተፀንሶ የተወለደው ኢየሱስ ክርስቶስ ነው።
ሙሴን ወደ ተራራው እንዲወጣ ያስገደደው የተራራው ምስጢር ዛሬ በፊታችን ተገልጧል። ሐመልማሉ ነበልባሉን እንዴት አላጠፋውም? ነበልባሉስ ሐመልማሉን እንደምን አላቃጠለውም? እያልን በእግረ ሕሊና ከሙሴ ጋር ወደ ደብረ ሲና ስንጓዝ ለዘመናት ኖርን፤ ያንን ድንቅ ምስጢር የሚያስረዳ ታላቁ ምስጢር እነሆ በፊታችን ነው።
የመለኮት እሳት ሰውነቷን አላቃጠለውም፤ ሰውነቷም እሳተ መለኮትን ለመሸከም የተገባው ሆነ።
ሙሴ በደብረ ሲና ያያትን ዕጽ ለማየት ዛሬ ወደ ቤተ ልሔም እንሄዳለን። እንደ አባ ሕርያቆስም “ኦ ድንግል ሶበ ሐደረ ውስተ ከርስኪ እሳተ መለኮት እፎኑ ኢያውአየኪ፤ ድንግል ሆይ የመለኮት እሳት በማህጸንሽ ባደረ ጊዜ እንዴት አላቃጠለሽም” እያልን እናመስግናት።
የሲና ሐመልማል ርጥበቷ ያላጠፋው እሳት ልጇ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። እሳቱ ያላቃጠላት እጸ ጳጦስ የጌታ እናቱ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ናት።
እንደ ልማዳችንስ ቢሆን የእንጨቱ ርጥበት እሳቱን ባጠፋው፣ የእሳቱም ውዕየት እንጨቱን ባቃጠለው ነበር።
ዛሬ ግን ከዚያ የተለየ ድንቅ ምስጢር እያየን ነው።
የመለኮት እሳት ሳያቃጥላት የታቀፈችው እመቤታችን በዚህ አለች። የሥጋን ልብስነት የለበሰ እሳት በእመቤታችን ዕቅፍ ተቀምጦ አለ።
ሙሴ የደብረ ሲናውን ምስጢር ሊያደንቅ በጎቹን ትቶ ወደ ተራራው እንደወጣ እኛም ዛሬ አማናዊት እጸ ጳጦስ እመቤታችንን ለማየት ወደ ቤተ ልሔም እንወጣለን።
የደብረ ሲናው ምስጢር በቤተ ልሔም ተተረጎመ።
እንኳን አደረሰን አደረሳችሁ መልካም በዓል