እረኞች በምስጋና የተቀበሉት መልካሙ እረኛ ኢየሱስ ክርስቶስ ዛሬ ስለ መልካም እረኝነቱ ቤተ ክርስቲያን ታመሰግነዋለች።
እንደዚህ ያለ እረኛ የት ይገኛል? ሕዝቡን ይጠብቃቸው ዘንድ ወደ ዓለም በመምጣቱ እረኛችን እንለዋለን እንጂ እንደምናውቃቸው እረኞች ያለ ባሕርይ የለውም።
የዚህ ዓለም እረኛ ሲጠብቅ ኖሮ ከተኵላ ቢያድነውም ራሱ አርዶ ይበላዋል። ከሌባ ጠብቆ ቢያድነውም ራሱ ይሸጠዋል። ከበላተኛ የሚጠብቀው ራሱ ሊበላው ነው። ተንከባክቦ የሚያሳድገው ኑሮው በሚጠብቀው በግ ላይ ስለተመሠረተ ነው።
እውነተኛውን የበጎች እረኛ ክርስቶስን ግን ተመልከቱት! ከእነዚህ አንዱንም ጠባይ አታገኙበትም።
በጎቹ የሚበሉት እረኛ ከሱ በቀር ማን አለ? ራሱ ተሽጦ መንጋውን ያለ ዋጋ ከመሸጥ የሚያድን እረኛ ልናገኝ እንችላለን? መንጋው ስለ እረኛው ይሸጣል እንጂ እረኛ ስለ መንጋዎቹ ሲሸጥ ያየነው በክርስቶስ ነው።
የበጎቹን ጸጉር ሸልቶ የሚለብስ እረኛ ሞልቷል፤ ለበጎቹ ልብስ የሚሆን እረኛ ግን ክርስቶስ ብቻ ነው። በጎቹን የጽድቅ ልብስን አለበሳቸው።
በጎቹን ሌባ እንዳያገኛቸው ነጣቂ ተኵላ እንዳይበላቸው አስገብቶ ይዘጋባቸውና ወደ ቤቱ ገብቶ የሚተኛ እረኛ በእኛም ዘንድ ነበረ። በጎቹን እሱ ወደ አለበት ወደ ገነት ሰብስቦ ይዞ የሚገባ እረኛ ግን ክርስቶስ ብቻ ነው ሉቃ. 23፥44።
በጎቹ ቢጠፉበት ፍለጋ የሚወርድ እረኛ ፈልገን ላናጣ እንችላለን፤ የጠፉ በጎቹን ባገኛቸው ጊዜ በትክሻው ተሸክሞ የሚያመጣ እረኛ ከእርሱ በቀር ማን ይገኛል?
ከመቅደሱ ለጠፉ በጎች እባካችሁ ንገሯቸው! ክርስቶስ እናንተን ፍለጋ ወደ ዱር ወርዷል ቢያገኛችሁ በትክሻው ይሸከማችኋል በሏቸው። ጠፍተው የተገኙ በጎች ምንኛ የታደሉ ናቸው? ሁሉን በሚችል ትክሻው የተሸከማቸው፣ ወደ መቅደሱም የመለሳቸው።
ጠፍተው ለተገኙ በጎቹ ጎረቤቶቹን ጠርቶ ቤተ ሰቦቹን ሰብስቦ ታላቅ ደስታ ያደረገ ከእርሱ በቀር የምናውቀው የለንም ሉቃ. 15፥10።
ከእንግዲህ ወዲህ ኃዘን የለንብም፤ በዕረፍት ውኃ በለመለመ ሳር የሚያሰማራንን እረኛችንን አግኝተነዋልና መዝ. 22፥1። መከራም የለብንም ስለእኛ መከራን ሁሉ ሊቀበል በፊት በፊታችን የሚሄድልን እረኛ ተሹሞልናልና።
ነፍሳችንን ሊያድናት ነፍሱን ስለኛ የሚያኖር እረኛ እያለን እኛ ምን ያስጨንቀናል? ዮሐ. 10፥11።
እኛስ ድምጹን እንሰማለን፤ በፊት በፊታችን የሚሄደውምንም መልካም እረኛ እንከተላለን።
“ወደ ነፍሳችሁ እረኛ ተመልሳችኋል” 1ጴጥ. 2፥25